2023-12-12 17:14:09
የአማራ ክልል መንግስት የሰላም ጥሪ አስተላለፈ!
የአማራ ክልል መንግስት ከኃይል አማራጭን በመተው ወደ ሰላም ለሚመለሱ ኃይሎች የሰላም ጥሪ አስተላልፏል።
የክልሉ መንግስት ያወጣውን የሰላም ጥሪ አስመልክቶ የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር መንገሻ ፈንታው መግለጫ ሰጥተዋል።
የሰላም ጥሪው ተጨማሪ ደም መፋሰስን ለማስቀረት መንግስት በሆደ ሰፊነት የከፈተው የሰላም በር ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በጽንፈኝነት የተቃኘ እና የግል ፍላጎትን ማዕከል ያደረገ አላማ ባነገቡ ጥቂት ግለሰቦች እና ቡድኖች ቅስቀሳ የተሳሳቱ ወጣቶች እና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ከስህተት መንገድ የሚመለሱበትን ሰላማዊ መንገድ ማመቻችት ስለሚገባ፤ በክልሉ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ከህዝብ ጋር በተደረጉ ተከታታይ ውይይቶች የህግ የበላይነትን ባረጋገጠ አግባብ ለታጣቁ አካላት የሰላም ጥሪ ቀርቦ ግጭቱ እንዲያበቃ እና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ከህዝብ የተነሳውን ጥያቄ በመቀበል፤ ተጨማሪ ደም መፋሰስን፣ጥፋትን እና ውድመትን ለማስቀረት መንግስት በሆደ-ሰፊነት የሰላም አማራጮችን አሟጦ የመጠቀም ጥረቱን ማስቀጠል ለሃገር እና ለህዝብ ያለውን ጠቀሜታ ከግምት በማስገባት፤ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መመርያ ዕዝ ጋር በመመካከር ስምምነት በተደረሰበት አቅጣጫ እና የሕዝብን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የወጣውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6 /2015 አንቀጽ 5(4) (ሠ) እና 6(12) መሰረት በማድረግ ይህ የሰላም ጥሪ የውሳኔ ሃሳብ ተላልፏል ሲል በመግለጫው አስታውቋል።
የውሳኔ ነጥቦቹንም እንደሚከተለው ጠቅሷል፣
1) ይህ ጥሪ ለህዝብ ይፋ ከተደረገ ጀመሮ በሚቆጠር ሰባት ቀናት ውስጥ በየትኛውም ኢመደበኛ አደረጃጀት እና ትጥቅ ትግል ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ ታጣቂዎች ባሉበት አካባቢ በሚገኙ የኮማንድ ፖስት አዛዦች ለዚሁ አላማ ለይተው ለህዝብ ወደሚያሳውቋቸው የመሰብሰቢያ ስፍራዎች በመሄድ ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመመለስ ያላቸውን ፍላጎት እንዲያሳውቁ ጥሪ ቀርቧል።
2) በየአካባቢው ያሉ የቀጠና ኮማንድ ፖስት አመራሮች፣ የአካባቢው አስተዳደር እና የፖለቲካ አመራሮች እንዲሁም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች እና የሃገር ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመመለስ ፍላጎት ኖሮዋቸው ወደ መሰብሰብያ ስፍራዎች ከላይ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የሚመጡትን ሁሉ በአግባቡ በመቀበል፣ የህክምና አገልግሎት እና መሰል አጣዳፊ አገልግሎት ለሚያስፈልጋቸውም አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ እንዲያስተናግዱ እና ወደተሃድሶ ማዕከላት እንዲወሰዱ መመሪያ ተሰጥቷል።
3) የቀጠና ኮማንድ ፖስት አመራሮች እና ተሃድሶ ማዕከላት አስተባሪዎች ወደ ሰላማዊ ኑሮ የሚመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሃድሶ ማዕከላት ውስጥ አስፈላጊውን የተሃድሶ ስልጠና እንዲያገኙ፣ ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው በሰላም ለመኖር የሚያስችላቸውን የአዕምሮ ዝግጅት ለማድረግ አስፈላጊው የሰነ-ልቦና፣ ምክር እና ሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በማድረግ የተሃድሶ መርሃ ግብር መጨረሳቸውን እያረጋገጡ የምስክር ወረቀት እንዲሰጡ መመሪያ ወርዷል።
4) ለህግ እና ፍትህ አካላት የተሃድሶ መርሃግብር ማጠናቀቂያ የምስክር ወረቀት ያገኙ የቀድሞ ታጣቂዎች በግጭቱ አውድ ውስጥ የተፈፀሙ በምህረት ሊሸፈኑ የሚችሉ ወንጀሎችን በተመለከተ የምህረት ተጠቃሚ እንደሆኑ በመገንዘብ እነዚህ ግለሰቦች ላይ ከነዚህ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ የተጀመሩ የምርመራ፣ የክስም ሆነ የፍርድ ማስፈፀም ሂደቶችን በማቋረጥ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉ መመሪያ ተላልፏል።
5) የክልል፣ ዞን፣ ወረዳ እና ቀበሌ የፖለቲካ፣ የአስተዳደር አካላት እና አመራሮች ይህን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለሚመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ኑሮ መመለስ እንዲችሉ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉ፣ በተለይም እነዚህ ዜጎች በሰላማዊ እና ህጋዊ አግባብ የፖለቲካ ግብ እና አጀንዳቸውን ማራመድ ይችሉ ዘንድ ምቹ አውድ እና የውይይት መደረኮችን እንዲያመቻቹ መመሪያ ተሰጥቷል።
6) ይህንን የሰላም ጥሪ በየደረጃው ካሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እዞች ወይም ኮማንድ ፖስቶች ጋር በመቀናጀት እንዲያስፈፅም እና ለአፈፃፀሙ አስፈላጊ የሆኑ ዝርዝር መመሪያዎችን እንዲያወጣ ለክልልሉ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊነት እና ስልጣን ተሰጥቷል።
7) የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መመሪያ እዙ ጋር በመተባበር ይህ የሰላም ጥሪ ተግባራዊ ሆኖ በክልሉ ግጭት እና ሁከት እንዲቀር፣ህዝብም እፎይታ እንዲያገኝ ያለውን ቁርጠኝነት እየገለፀ ለዚህ ጥሪ ውጤታማነት አስተዋፅዖ ሊያበረክቱ የሚችሉ ባለድርሻ አካላት ሁሉ፣በተለይም የሃገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ለሰላም አጀንዳው መሳካት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪውን ያቀርባል።
በዚሁ አጋጣሚ ይህን ጥሪ ቸል በማለት የአመፅ እና የጉልበት መንገድ በሚመርጡ ግለሰቦች እና ታጣቂዎች ላይ የተጀመረው የህግ ማስክበር እርምጃ ተጥናክሮ እንደሚቀጥል ለማሳወቅ እንወዳለን ሲል ገልጿል።
@
Addis_Mereja
14.1K viewsedited 14:14