2023-06-30 16:48:55
+ ገነትና ሦስት ነገሮች +
በጎ የምትሠራው ለምን ብለህ ነው? ለመጽደቅ? ላለመኮነን? ወይንስ በጎ ስለሆንክ? ለደሃ የምትመጸውተው ከሲኦል ለመዳን ነው? ገነት ለመግባት ነው? ወይስ ለደሃው አዝነህ?
ቅዱስ ባስልዮስ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚገቡ ሦስት ዓይነት ሰዎች አሉ ይልሃል::
የመጀመሪያዎቹ "ሠራተኞች" ናቸው::
ሠራተኛ የሚሠራው ለደሞዝ ብሎ ነው:: አንዳንድ ሰዎች ሁልጊዜም ገነት ለመግባት ሲሉ በጎ ሊሠሩ ይችላሉ:: "የነፍስ ዋጋ አድርግልኝ" እያሉ የሚመጣውን ሕይወት ተስፋ አድርገው ለተሻለው ሲሉ አሁን ዋጋ ይከፍላሉ:: "ከሩቅ አይተው ተሳለሙት ሀገራቸው እንደሆነችም አወቁ" እንዲል የተስፋይቱን ሀገር ብለው በጎ ይሠራሉ:: ከበጎነታቸው ጋር ደሞዝ ፍለጋ አለበትና ቅዱስ ባስልዮስ ሠራተኞች አላቸው::
ሁለተኛዎቹ "ባሪያዎች" ናቸው::
እንደሚታወቀው በባርነት ዘመን ባሪያ ንብረትነቱ የጌታው ነውና ለሥራው ደመወዝ የለውም::
የሚሠራው በዋነኝነት ቅጣት ፈርቶ ነው:: በአግባቡ ሠርቶ ጌታውን ካላስደሰተ ግርፋት ይደርስበታል::
አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ለበጎ ሥራቸው ምክንያቱ "ሲኦልና ገሃነምን" መፍራት ነው::
"ያንን እሳት አታሳየኝ" "ምረረ ገሃነም እንዴት ይሆን?" እያለ በጎ የሚሠራ ሰው ነው::
ይህ ሰው በጎነቱ ገሃነምን ከመፍራት ስለሚመነጭ ቅጣት ፈሪ ነውና ቅዱስ ባስልዮስ ባሪያ ይለዋል::
ሦስተኞቹ ልጆች ናቸው::
ከገሃነም ፍርሃትና ከመንግሥቱ ጣዕም ሌላ የበጎነት ምክንያታቸው ልጅነት ነው::
ልጅ በአባቱ ቤት ሲሠራ ደሞዝ የለውም::
ባለመሥራቱም የባሪያ ቅጣት የለበትም:: ልጅ ስለሆነ ብቻ በደስታ በጎ ይሠራል:: ሲሠራም እንደ ጠፋው ልጅ ወንድም "እንደባሪያ ተገዛሁ" ብሎ አይማረርም:: "አንድ ጠቦት እንኳን አልሠጠኸኝም" ብሎ ስለ ደመወዝ አይከራከርም:: የአባቴ የሆነ ሁሉ የእኔ ነው ብሎ ያምናል:: ስለዚህ በጎ የሚሠራው ከልጅነቱ በመነጨ ደስታ ነው::
በጎ ሥራን ከፍርሃትም ከዋጋ መሻትም በላይ በደም ሥራቸው ጠልቆ የፈጣሪ ፈቃድ ፈቃዳቸው ሆኖ የሚሠሩት አሉ::
"ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም
ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም" በሚል ከበደ ሚካኤላዊ ጠርጣራነት (skepticism) ገነትና ሲኦል ላይኖር ይችላል ብለው አይደለም::
"እግዚአብሔር አለ ብለን አምነን እግዚአብሔር ባይኖር ምንም አናጣም:: እግዚአብሔር የለም ብለን አምነን እግዚአብሔር ቢኖር ግን ሁሉን እናጣለን" (If God does not exist, one will lose nothing by believing in Him, while if he does exist, one will lose everything by not believing) በሚል Blaise Pascaላዊ ቴዎሪ አስልተውም አይደለም:: አባታቸው እግዚአብሔር በጎ ሥሩ ያለበት መንሥኤ ገብቶአቸው:: በጎ መሥራት ምግብ መጠጣቸው እስትንፋሳቸው ሆኖ በጎ አለመሥራት የሚሳናቸው ሆነው በጎ የሚሠሩ ሰዎች አሉ::
እነዚህን ቅዱስ ባስልዮስ ልጆች ይላቸዋል::
ሦስቱም ክብሩ ይለያይ እንጂ ለመንግሥቱ ይደርሳሉ:: አንዱ አንደኛውን ሊንቅ ሊስቅበት አይገባም:: ክርስትናንም ከሦስት በአንዱ ውስጥ ብቻ ከትቶ መደምደም አይገባም::
ሌላው አባት ደግሞ ገነት ገብቶ ያየውን ሦስት በጣም ያስደነቀውን ነገር ለሌላ አባት በሕልም ተገልጦ እንዲህ ሲል ነገረው::
ሦስት ነገር አስደነቀኝ
አንደኛው :- ገነት ውስጥ በፍጹም አገኛቸዋለሁ ብዬ የማልጠብቃቸውን ሰዎች በገነት ማግኘቴ
"ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል" ማቴ 21:31
ሁለተኛው :- ገነት ውስጥ አገኛቸዋለሁ ብዬ የምጠብቃቸውን ሰዎች አለማግኘቴ
"ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል" 1ኛ ሳሙ 16:7
ሦስተኛው :- እኔ ራሴን ገነት ውስጥ ማግኘቴ
"አቤቱ አምላክ ሆይ፥ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ?" 1ኛ ዜና 17:16
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ኅዳር 14 2013 ዓ ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
ፎቶ :- ደራሲ ወሐያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ ከፌስቡክ ሲዘዋወር የተገኘ
ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ!
ሌሎች እንዲያነቡትም ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች #share አድርጉ
1.5K viewsመርጌታ መንግስቱ ባህላዊ መድሀኒት ቀማሚ, 13:48