Get Mystery Box with random crypto!

#Repost በአሁኑ ጊዜ እንዴት የሰው ልጅ በማይታይ ፈጣሪ ሊያምን ቻለ ? በሚለው ጠቅላይ እን | ከፍልስፍና ዓለም

#Repost

በአሁኑ ጊዜ እንዴት የሰው ልጅ በማይታይ ፈጣሪ ሊያምን ቻለ ? በሚለው ጠቅላይ እንቆቅልሽ ዙሪያ ሶስት አንኳር ንድፈ-ሀሳቦች በስፋት ይቀነቀናሉ። እነዚህም :-

1) ግለኛ ንድፈ-ሀሳብ (Subjective theory)  2)የዝግመተ ለውጥ ሀሳብ (Evolution theory) እና 
3) የአሀዱ አምላክ ንድፈ ሀሳብ (original monotheism theory) ናቸው


1 )ግለኛ ንድፈ-ሀሳብ (Subjective theory)

በዚህ ንድፈ  ሀሳብ እምነት መሰረት ሃይማኖት ከሰዋዊ (ግለሰባዊ) ተፈጥሮ የሚመነጭ ነው ሰዎች በዚህ ውጥንቅጡ በወጣና በጥያቄዎች በተሞላ ምድር ተስፋና ትርጉም የሚጭርባቸውን ሀይማኖትን መፍጠር ግላዊ ስነ-ልቦናዊ ተፈጥሯቸው ያስገድዳቸዋል የዚህ ንድፈ-ሀሳብ አቀንቃኞች እንደሚሉት ይህ የእምነት ስሪት ቅንጣት (religious element) ልብ በማንለው የአእምሯችን ክፍል ያለ ፍቃዳችን በራሱ ጊዜ የሚፈጠር ነው ባህልና አስተሳሰብ ከቦታ ቦታ ይለያያል። ፈጣሪን መፈለግና እምነትን ማበጀት ግን ሰዋዊና ዓለም አቀፋዊ ተፈጥሮ ነው:: ሲያጠቃልሉም ! ይህ ሀይማኖትን የማበጀት ተግባር ሰዎች በግላችን ከባህልና ከአካባቢያችን የምንቀዳው ይመስለናል እንጂ እውነተኛ መፍለቂያው ግን ከግላዊ የአእምሯችን ጓዳ ነው
ፍሬድሪክ ሼሬልማኬር የዚህ ንድፈ ሀሳብ ሁነኛ አቀንቃኝ ሲሆን ሀይማኖት ከሰው ልጅ የጥገኝነት ባህሪ የሚፈልቅ ነገር እንደሆነ ይሞግታል የሰው ተፈጥሮና ፍላጎት ምሉዕ ስላልሆኑ ለዚህ የምሉዕነት ስብዕና ፍላጎትና ናፍቆት አጋዥ የሚሆን አካል ያስፈልገናል ያን ፍላጎታችንን ፈጣሪ (God) ለሚባል ነገር አስተላለፍነው ይለናል፡፡
ሌላው ሉድዊ ፈርባች የተባለ ተመራማሪ እንደሚለው ደግሞ ፈጣሪ የሚለው ፅንስ - ሀሳብ ፍፁም ሰብ (perfect human) ከመፈለግ የመነጨ ነው ሲግመን ፍሮይድም ተቀራራቢ ትንታኔን ይስጣል እንደ ፍሩድ እምነት የፈጣሪ በሰዎች መፈጠር መነሻቸው ፍፁም ምሳሌ ኣባት (father irnage) ከመሻቱ ጋር የተሳሰረ ነው ይለናል።

2. የዝግመተ ለውጥ ንድፈ-ሀሳብ (Evolution theory)

ይህ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኝ ንድፈ-ሀሳብ ልክ እንደ ግለኛ (subjective) ሀሳብ አቀንቃኞች ሁሉ የሀይማኖት ምንጭ የሰው ልጅ ልቦና እንደሆነ ቢቀበልም የሀይማኖት እድገትና ሰፊ ቅቡልነት የተረጋገጠው ግን በሰው ልጅ የታሪክ መስተጋብር ዝግመተ ለውጥ ሂደት ነው ብሎ ያምናል  በቀደምት ጥንታዊ ሰው ዘንድ አንድ » ጉልበት ያለው መንፈስ እንዳለ ጥርጣሬ ነበረ፡፡ ይህ ሀይል ግን ጨካኝና ተፈጥሮን .... አንበርክኮ የሚገዛ እንደሆነ ያምኑ ነበር ከማሌኔዥያ ጥንታዊ ህዝቦች ስያሜ በመነሳትም ለዚህ ወዳጃዊ ላልሆነ መንፈሳዊ ሀይል «ማና» (Maana) የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል ማና በብዛት ሊገኝባቸው የሚችሉ ቦታዎች እንዳሉም ይታመን ነበር ለምሳሌ በታላላቅ ዛፎች በተለያዩ ዓለቶች በውስን የእንስሳት ዝርያዎች ወዘተ በብዛት ተከማችቶ ይገኛል ተብሎ ይታመን ነበር የጥንቱ ሰው ዓላማ የነበረው ይህን ጠንካራ መንፈስ (ማና) ላኑሮአቸው በሚመች መልኩ እንዲያግዛቸው ማድረግ ነበር  በኋላም ይህን መንፈስ በጣኦታትና በተወሰኑ የተፈጥሮ ሀይሎች ብቻ እንዲቀመጥና እንዲመለክ አደረጉ፡፡ ቀጣዩ ደረጃ ደግሞ ይህን መንፈስ ሰዋዊ ማድረግ ነበር የተወሰኑ ሰዎች ላይ ይህ መንፈስ እንደተገለጠላቸው ታመነ ይህም አኒሚዝም (Animism) ይባላል እየቆየ ሲሄድ መንፈሱ የሚያርፍባቸው ሁለት ጎራዎች ተለዩ የተፈጥሮ መንፈስ (nature spirit) እና የቅ/አያቶች መንፈስ (Ancestor spirit) ናቸው
የተፈጥሮ መናፍስት ሰዋዊ ገጽታ ያላቸውና በተክሉች፣ በዓለቶች፣ በሀይቆች ወዘተ ራሳቸውን ተቀማጭ ያደረጉ ናቸው የቅ/አያቶች መንፈስ ግን በጣኦታት ወይም ባሉና በሌሉ ሰዎች ሊወከል ይችላል ስለዚህ እነዚህ ሁለት አይነት መናፍስት ተቆጥተው ሊያደርሱ ከሚችሉት አደጋ ለመጠበቅ ጥንታዊው ሰው ከመናፍስቱ ጋር መልካም ወዳጅነትን ለመመስረት ጣረ
በዝግመተ - ለውጡ ሂደት መሰረት በብዙ አማልክት ( መናፍስት) ማመን (polytheism) ቀጥሎ የሚመጣ ደረጃ ነው በተለያዩ መናፍስት አማኝ የነበሩ ህዝቦች ቀስ በቀስ የብዙ መናፍስትን ወካይ በሆኑ አማልክት (ጣኦታት) ተገዙ  ቀጠሉና በሂደት ከአማልክቶቹ ውስጥ ለተወሰኑቱ አማልክት ብቻ መገዛት (henotheism) ደረጃ ተደረሰ፡፡ በዚህ ደረጃ ሁሉም አማኝ ለብዙ (ለተወሰኑ) አማልክት ይምበርከክ እንጂ ጥያቄው በነዚህ አማልክት ውስጥ ትልቁን አንድ አምላክ ማግኘት ነበር በመጨረሻም ከረጅም ዝግመታዊ የአምልኮ ሂደት በኋላ በአንድ ፍፁምና ጠቅላይ አምላክ ማመን (monotheism) ተሸጋገረ ይህም ሀይማኖት ተፀንሶ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ሲሆን ወደ ፊት ደግሞ በዝግመተ- ለውጥ (Evolution) ሌላ መልክና ይዘት እንደሚይዝ ይጠበቃል፡፡

3) የአሀዱ አምላክ ንድፈ-ሀሳብ (Original Monotheism)

ይህ ንድፈ - ሀሳብ የብዙ ሀይማኖቶችን አቋም የሚያንፀባርቅ ሲሆን እምነት የመነጨው ፈጣሪ ራሱን ለሰው ልጅ ስለገለፀ ነው የሚል መቋጫ ያስቀምጣል፡፡ በዚህም መሰረት ጥንታዊው የሰው ልጅ የመጀመሪያው እምነት አሀዳዊ አምልኮ (monotheism) ነበር ሲል ይሞግታል፡፡ የዚሁ ንድፈ - ሀሳብ አቀንቃኝ ከሆኑት መሀል ዶ/ር ዊንፍሬድ ኮርዶን የጥንታዊው ሰው እምነት መገለጫ ነበሩ ያላቸውን ዘጠኝ ባህርያት አስቀምጧል፡፡ እነዚህም

1) ፈጣሪ ሰዋዊ አምላክ ነው (ወዳጃዊ ያልሆነ ነው ብለው ያምኑ ነበር ከሚሉት በተለየ መልኩ

2) ፈጣሪ ተባዕታይ ይዘትና መገለጫዎች አሉት
3) ፈጣሪ ነዋሪነቱ በሰማይ ነው፡፡
4) ፈጣሪ ታላቅ ጥበብና ሀይል አለው
5) ፈጣሪ መልካምና እኩይ ብሎ ለነገሮች ክፍፍል ሰጥቷል
6)ፈጣሪ ዓለምን ፈጥሯል
7) የሰው ልጆች የተፈጠሩት በፈጣሪ ስለሆነ የሱን ፍላጎት መከተል አለባቸው
8) የሰው ልጆች ከፈጣሪ አፈንግጠዋል
9) ፈጣሪ የሰው ልጆች ከሀጥያት የሚነፁበትን መንገድ አበጅቶላቸዋል የሚሉት ናቸው፡፡

የጥንታዊ ህዝቦች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ እነዚህን ዘጠኝ ነጥቦች በአምል ኳቸው አንፀባርቀው እንደነበረ የሚሞግቱት የዚህ ንድፈ-ሀሳብ አቀንቃኞች ከዚህ ፍፁም አህዳዊ አምልኮ ተነስተው የሰው ልጆች ወደ ብዙ አማልክት ማመን (polytheism) እና በፈጣሪ ጭራሽ አለማመን (Atheism) እንደተሸጋገሩና እንደተሰነጣጠቁ ያስረዳሉ ለዚህ ትንታኔአቸው አስረጅ አድርገው የሚያቀርቡት አሁን በዓለም ላይ ያሉ ሁሉም ሀይማኖቶች ታሪኮቻቸው የፀሎት ስርዓታቸው ቀኖናቸው ወዘተ መመሳሰል የዚሁ ከአንድ ምንጭ መቀዳታቸው ነፀብራቅ እንደሆነ አስረግጠው ይናገራሉ

ዳሰሳ ዘ ሀይማኖት