Get Mystery Box with random crypto!

በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የቤት ኪራይ እንደሚጨምር ተገልጿል - የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስ | Ethiopian Digital Library

በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የቤት ኪራይ እንደሚጨምር ተገልጿል - የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ ጸደቀ

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 3ኛ የሥራ ዘመን 19ኛ መደበኛ ስብሰባ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅን አጸደቀ።

በዛሬው ዕለት በሦስት ድምጽ ተአቅቦ ያለተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ የጸደቀው አዋጅ ቁጥር 1320/2016 በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ተስፋዬ በልጂጌ ማብራሪያ ሰጥተውበታል። የመንግስት ዋና ተጠሪው በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት እና ፍላጎት የተጣጣመ እንዳልሆነ ገልጸው በዚህ ሳቢያ ምክንያታዊ እና ፍትሃዊ ያልሆነ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪዎች በአገሪቱ ይስተዋላል ብለዋል።

ተስፋዬ በልጂጌ ለምክር ቤት አባላቱ እንዳስረዱት ነባራዊ ሁኔታው እና የዜጎች እሮሮ በመኖሪያ ቤት ኪራይ ላይ የመንግስት አስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ በመሆኑ ይህ አዋጅ ተዘጋጅቷል። የአዋጁ ዋና ዓላማ ግልጽና ተገማች የሆነ የመኖሪያ ቤት ኪራይ አስተዳደር መዘርጋት እንዲሁም የአከራይ እና ተከራይ መብትን ሚዛናዊ ለማድረግ እንደሆነ ተገልጿል።

ስድስት ክፍሎችና 32 አንቀጾች አሉት። በውስጡ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል እና ዋጋ፣ የአስፈጻሚ አካላት ስልጣን እና ሌሎች ድንጋጌዎች እንደተካተቱበት ተገልጿል።

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ ክፍል 2 አንቀጽ 8 ላይ የዋጋ ጭማሪን በተመለከተ ከዚህ በፊት አከራዮች በፍላጎታቸው የሚጨምሩትን ገንዘብ ተከራዮች በግዴታ መቀበል ቢኖርባቸውም፤ አሁን በመንግስት ተቆጣጣሪ አካል ጣልቃ ገብነት በዓመት አንድ ጊዜ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታና የኢኮኖሚ ሁኔታ ታይቶ በመቶ በሚሰላ ጭማሪ ፈቃድ ብቻ የቤት ኪራይ እንደሚጨምር ተገልጿል።

በተጨማሪም የቤት አከራዮች ቅድመ ክፍያ መጠየቅ የሚችሉት የሁለት ወር ብቻ እንዲሆን የሚደነግግ ሲሆን ተከራዮችን ለማስለቀቅም የሁለት ወራት የዝግጅት ጊዜ እንዲሰጥ ያስገድዳል። ከዚህ ባለፈም መንግስት ማግኘት ያለበትን ግብር እንዲያገኝ እንደሚያስችል የምክር አባላት ተናግረዋል።

አዋጁ በተለምዶ ለአከራዮች ሰፊ እድልና መብት የሚሰጠውን ስርዓት ለማመጣጠን ያግዛልም ተብሏል።

ነምቤኦ (NUMBEO) የተባለ በሰርቢያ አገር መቀመጫውን ያደረገ የአገራትን የኑሮ ደረጃ የሚመዝኑ መረጃዎችን የሚያጋራ ድረ ገጽ የአገራቱን ዜጎች ገቢ እና የመኖሪያ ቤት ዋጋ ጥምርታን በማነጻጸር ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያውያን ለመኖሪያ ቤት የሚያወጡት ዋጋ ከገቢያቸው ላይ 43 ነጥብ 1 በመቶ እንደሆነ ተመላክቷል። #አዲስ_ማለዳ

@Ethiopian_Digital_Library
@Ethiopian_Digital_Library