Get Mystery Box with random crypto!

ብር የወሰዱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች Bitcoin ጨምሮ ሌሎች ውድ እቃዎችን በመግዛታቸው ብሩን ለመመ | Ethiopian Digital Library

ብር የወሰዱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች Bitcoin ጨምሮ ሌሎች ውድ እቃዎችን በመግዛታቸው ብሩን ለመመለስ የተቸገሩ ተማሪዎች በርካታ ናቸው

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የገንዘብ ዝውውሩ ላይ ችግር ባጋጠመው ጊዜ በርካቶች ከገንዘብ መክፈያ ማሽኖች ላይ እንዲሁም በሞባይል ባንኪንግ አማካይነት በሂሳባቸው ካላቸው የገንዘብ መጠን በላይ ማንቀሳቀስ ችለዋል።
ባንኩ እንደሚለው በዚያ ወቅት ከአስር ሺህ በላይ ግለሰቦች ከ490 ሺህ በላይ የገንዘብ ዝውውር አድርገዋል። በዚህ ሂደትም አንዳንዶች እንደሚሉት ከሚሊዮኖች እስከ ቢሊዮን መጠን ያለው ብር ተንቀሳቅሷል።

በዚህ ሁኔታ ያላሰቡትን ገንዘብ ያዘዋወሩ ተማሪዎች ብሩን የተለያዩ ውድ ቁሶችን መግዛታቸውን እና ለሌሎች ሰዎች ማስተላለፋቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተማሪዎች ገልጸዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲው ተማሪ እንደሚለው ብዙ ጓደኞቹ በወሰዱት ገንዘብ የተለያዩ ውድ ነገሮችን በመግዛታቸው ገንዘቡን መልሰው ማግኘት በማይችሉበት ሁኔታ ላይ ስላሉ ጭንቀት ላይ ይገኛሉ ይላል።
በተለይ ላፕቶፕ እና ዘመናዊ ስልኮችን የገዙ ተማሪዎች ጥቂት አለመሆናቸውን የሚጠቅሰው ተማሪው “100ሺህ ብር የሠራ አንድ ልጅ በሁለተኛው ቀን ላፕቶፕ እና ስማርት ስልክ ገዝቷል” በመግዛቱ እጁ ላይ የሚመልሰው ገንዘብ እንደሌለ ገልጿል።

“ሌሎች ደግሞ ያልተገደበ የአንድ ዓመት የኢንተርኔት ጥቅል ገዝተዋል። የነበረባቸውን ብድር የከፈሉ አሉ። . . . ብዙዎቹ ገንዘቡን ተጠቅመውበታል።”
ቢቢሲ ያነጋገረው ሌላ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሲስተም ችግር ባጋጠመበት ሌሊት ጓደኞቹ በተደጋጋሚ እየደወሉ ገንዘብ ወጪ እንዲያደርግ ቢነግሩትም “ምንም አልሠራሁም” ይላል።

ነገር ግን የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ ለማውጣት የቻሉት ጓደኞቹ ወደ እርሱ አካውንት 50 ሺህ ብር ካዘዋወሩ በኋላ የባንክ ሂሳቡ መታገዱን ይገልጻል።
“ገንዘቡን ለላከልኝ ልጅ ልመልስ ብል እንኳን አካውንቴ ታግዷል። ፈልጌ አይደለም ገንዘቡ የተላከልኝ። ትራንስፈር ስለተደረገ አካውንቴ ተዘግቶብኛል” ይላል።

ቢቢሲ ያነጋገረው ሌላኛው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ገንዘብ መውሰዱን አምኖ የወሰደውን ለመመለስ ፍቃደኛ ቢሆንም አካውንቱ በመታገዱ ተመላሽ ማድረግ አለመቻሉን ይገልጻል።

ይህ ተማሪ በሞባይል ባንኪንግ አማራጭ ወደ 70 ሺህ ብር ወደ ሌላ ባንክ አካውንት ገንዘብ ማዘዋወሩን ነገር ግን “ከሰኞ ጀምሬ ለመመለስ ብጥርም አካውንቱ እንዳይንቀሳቀስ በመደረጉ አልቻልኩም” ይላል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ችግሩ ባጋጠመበት ጊዜ ከፍተኛ መጠን ያላቸው የገንዘብ ዝውውሮች መደረጋቸውን አመልክቶ፤ በወቅቱ ግብይት ሲፈጸምባቸው የነበሩ የባንክ ሂሳቦች ማጣራት እስኪደረግባቸው ድረስ እንዲታገዱ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ ባንኩ ካጋጠመው ችግር ጋር በተያያዘ የወሰዱ ሰዎች እስከ ነገ ቅዳሜ መጋቢት 14/2016 ዓ.ም. ድረስ እንዲመልሱ በድጋሚ ጠይቋል። በቀነ ገደቡ ያልመለሱትን ግለሰቦች ስምና ፎቶ በመገናኛ ብዙኃን ይፋ በማድረግ በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርግም አስጠንቅቋል።

በዚህም ምክንያት ገንዘቡን ወስደው የተጠቀሙበት እንዲሁም ወደ ታገዱ አካውንቶች ያዘዋወሩ ተማሪዎች “ድንጋጤ እና ጭንቀት” ውስጥ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ከባንኩ የወሰደውን ገንዘብ ወደ ሌላ አካውንት አዘዋውሮ ገንዘቡን ለመመለስ ተቸገርኩ ያለ ተማሪ በቅርቡ ፈተና እንዳለበት እና “ከክስተቱ ጋር በተያያዘ የስሜት መረበሽ ውስጥ እንደሚገኝ” ገልጿል። #ቢቢሲ
@Ethiopian_Digital_Library
@Ethiopian_Digital_Library