Get Mystery Box with random crypto!

ተረት ተረት - አህያ የበሉ መንገደኞች ከብዙ አመታት በፊት በድሮ ጊዜ መንገደኞች በጉዞ ላይ ብዙ | Ethiopian Digital Library

ተረት ተረት - አህያ የበሉ መንገደኞች

ከብዙ አመታት በፊት በድሮ ጊዜ መንገደኞች በጉዞ ላይ ብዙ ቀናትን ያሳልፉ ነበር፡፡ እንዳሁኑ ዘመናዊ መጓጓዣ ስላልነበረ ለሶስት፣ ለአራት አንዳንዴም ለአንድና ለሁለት ሳምንታት ያህል ከቦታ ወደቦታ እየተዘዋወሩ በጉዞ ላይ ያሳልፉ ነበር፡፡ ይህም ጉዞ በመንገዳቸው ላይ እንደሚያጋጥማቸው ሁኔታ ጊዜው ሊያጥር ወይም ሊረዝም ይችላል፡፡

ታዲያ በአንድ ወቅት አራት መንገደኞች በበረሃ እያቋረጡ ሳለ እጅግ በጣም ከመሞቁም በላይ በረሃብ ይቸገሩ ጀመር፡፡ በዚህም ምክንያት ካቀዱት ጊዜ በላይ በመንገድ ላይ ማሳለፍ ስለነበረባቸው ስንቃቸው አልቆባቸው የሚበሉት ነገር አጡ፡፡

በጉዟቸውም ላይ እየተዳከሙ ሄዱ፡፡

በበረሃውም ውስጥ የሚበሉት አጥተውና ሙሉ ለሙሉ ተዳክመው ቁጭ አሉ፡፡ በዚያች ቅፅበት ታዲያ ከየት እንደመጣ ያልታወቀ አንድ ግዙፍ አህያ እያናፋና በትእቢት እየሮጠ ወደ እነርሱ መጣ፡፡ በዚያ በረሃ ውስጥ አህያው ምን በልቶ እንደዚያ እንደጠገበ የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነበር፡፡ ሆኖም አህያው በጣም የጠገበ በመሆኑ እያናፋ ላይና ታች መሮጡን ቀጠለ፡፡

ታዲያ በደቡብ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ህዝቦች ክርስቲያን ስለሆኑ አህያን መብላት ይቅርና ለመብላት መፈለግም ጭምር በፍጹም የማይታሰብ ነበር፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ሸሆናቸው ድፍን የሆኑ እንስሳትን መብላት ይከለክል ነበርና ነው፡፡ ስለዚህ ስለሌሎች ጉዳዮች እየተወያዩ ቁጭ አሉ፡፡
ነገር ግን አህያው ማናፋቱን በመቀጠል የተለያዩ ድምጾችን እያሰማ ከፊታቸው መመላለሱን ቀጠለ፡፡ በዚህ ጊዜ አንደኛው ተጓዥ ቀና ብሎ አይቶ “ወንድሞች ሆይ፣ እዚህ በረሃ ውስጥ በረሃብ ከምናልቅ አህያውን በልተን ቢያንስ ወደ መንደራችን ብንመለስስ?” ብሎ ሃሳብ አቀረበ፡፡

ሌሎቹ ሶስቱ ተጓዦች ግን “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ! እንዴት እንደዚህ ያለውን ነገር ልታስበው ቻልክ?” አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሰውየው በድምፅ ብልጫ መሸነፉን አይቶ በዝምታ ቁጭ አለ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ሁለተኛው ተጓዥ ቀና ብሎ ሲመለከት የአህያውን ጮማና ጡንቻው ተፈልቅቆ ላይ ታች ሲሮጥ አይቶት “እኔ እስማማለሁ፡፡ ይህንን አህያ ካልበላን ሁላችንም እንሞታለን፡፡” አለ፡፡

ሌሎቹ ሁለቱ ግን በእምቢታቸው ፀንተው ቀሩ፡፡

ከዚያ አህያውን ለመብላት የተስማሙት ሁለቱ ተጓዦች አህያውን ይዘው ካረዱት በኋላ ጥጥ የመሰለ ጥሩ ጮማ ስጋና የተለያዩ ነገሮች እንዳሉት አዩ፡፡ አህያውንም ካረዱት በኋላ ትንሽ ጥሬ ስጋ በልተውለት ሌላውን የተለያዩ ምግቦች አዘጋጁበት፤ የተወሰነውን ጥብስ፣ ሌላውን ደግሞ ቅቅልና ሌሎች የተለያዩ የምግብ አይነቶችን አዘጋጁ፡፡ ምግቡንም በሚያዘጋጁበት ወቅት የስጋው ቅባት እየተንጣጣ የተለያዩ ድምጾችን በማሰማት ቹ፣ቹ፣ቹ፣ቹ,,,,,,,,ቹ፣ቹ፣ቹ,,,,, ሲል ሶስተኛው ተጓዥ ምራቁን ማዝረብረብ ጀመረ፡፡

በመጨረሻም ከዚህ በላይ የጮማውን አጓጉዊነት ታግሶ መቆየት ስላልቻለ አራተኛውን ተጓዥ “ና እባክህ! እኛም መብላት አለብን፡፡ ካለበለዚያ እዚህ በረሃብ እንሞታለን፡፡” አለው፡፡

አራተኛው ሰው ግን “እኔ የአህያ ስጋ በፍፁም አልበላም፡፡ ክርስቲያን በመሆኔ በክርስቲያንነቴ እሞታለሁ፡፡ አንገቴ ላይ ያሰርኩትም ማተብ የክርስቲያንነቴ መገለጫ በመሆኑ ለማተቤ ለመሞት ዝግጁ ነኝ፡፡” ብሎ አሻፈረኝ አለ፡፡

ሶስቱ ግን “አይ አንተ ሞኝ ሰው!” ብለው ተሳለቁበት፡፡ ይህንንም ብለው የአህያውን ስጋ በልተው ከጨረሱ በኋላ ጉልበታቸው ስለበረታ መንገዳቸውን ሊቀጥሉ ሲሉ አራተኛው ሰው እጅግ በጣም ስለተዳከመ ሰውየውን እየደገፉት በመጨረሻ ከመንደራቸው ደረሱ፡፡

ታዲያ መንደራቸው ከመግባታቸው በፊት አንዱ ሰው “እስኪ አንድ ጊዜ ታገሱ፡፡ አሁን ከመንደራችን ስንገባ አራተኛው ሰው እኛ የአህያ ስጋ እንደበላን ለመንደሩ ሰው ስለሚነግር ሰው ሁሉ ያገለናልና ምን ብናደርግ ይሻላል?” አለ፡፡

ሶስቱ ሰዎች ትንሽ ካሰቡ በኋላ አንደኛው “አንድ ሃሳብ አለኝ፡፡ እኔ አራተኛውን ሰው ‘የአህያ ስጋ በላ’ ብዬ ሳስወራበት እናንተ ሁለታችሁ ምስክር ትሆናላችሁ፡፡” አላቸው፡፡

እናም በዚህ ተስማምተው ወደ መንደሩ ዘለቁ፡፡

የመንደሩም ሰዎች ተጓዦቹ በሰላም ወደመንደሪቱ በመመለሳቸው ተደስተው ቡና ካፈሉላቸው በኋላ “በሰላም መመለሳችሁ መልካም ነው፡፡ በጣም ስለቆያችሁ የሞታችሁ መስሎን ነበር፡፡” አሉ፡፡

ትልቅ ድግስም ከተደረገ በኋላ ሁሉም ወደየቤታቸው ሄዱ፡፡ በሚቀጥለውም ቀን አንደኛው በስራ ላይ ወደነበሩት ገበሬዎች በመሄድ “አንድ ምስጢር ልንገራችሁ፡፡ ከሄድንበት አገር ወደዚህ እየተመለስን ሳለ እገሌ፣ የእገሌ ልጅ፣ የአህያ ስጋ በላ፡፡” አላቸው፡፡

እነርሱም “ይህ የማይሆን ነገር ነው! እንዴት እንደዚህ ያደርጋል? ይህ በጣም መጥፎ ነገር ነው፡፡” አሉ፡፡

ልክ በዚህ ጊዜ ሌሎቹ ሁለት መንገደኞች መጥተው “አዎን፣ ይህ አሳፋሪ ነው፡፡ እኛ በአይናችን አይተነዋል፡፡ የአህያ ስጋም በልቷል፡፡” ብለው በሃሰት መሰከሩበት፡፡

በዚያችው ቅፅበት ደግሞ አራተኛው ሰው ደርሶ “እንዴት እንደዚህ ብላችሁ ትናገራችሁ? እኔ የእገሌ ልጅ፣ የእገሌ ልጅ፣ የእገሌ ልጅ የአህያ ስጋ በፍፁም ልበላ አልችልም፡፡ ይህንን እናንተም ታውቁታላችሁ፡፡ እንዲያውም የአህያውን ስጋ የበላችሁት እናንተ ናችሁ፡፡” ብሎ ተናገረ፡፡

በዚህ ጊዜ የተሰበሰቡት ሰዎች “አይሆንም! እነዚህ ሶስት ሰዎች ሊዋሹ አይችሉም፡፡ እነርሱ የእገሌ ልጅ፤ የልጅ ልጅ፤ የእገሌ የልጅ፣ልጅ፣ ልጅ፤የእገሌ የልጅ፣ ልጅ፣ልጅ፣ልጅ ስለሆኑ ሃይማኖታቸውን ትተው የአህያ ስጋ አይበሉም፡፡” አሉ፡፡

በዚህ አይነት አራተኛው ሰው ከማህበረሰቡ ተገለለ፡፡ አንድ ሰው ከማህበረሰቡ ሲገለል ሴት ልጆቹ ባል አያገኙም፡፡ ወንድ ልጆቹም ሚስት አያገኙም፡፡ ስለዚህ ሰውየውና ቤተሰቡ ለዘለአለሙ ከማህበረሰቡ ተገለሉ፡፡

@Ethiopian_Digital_Library
@Ethiopian_Digital_Library