Get Mystery Box with random crypto!

ላልይበላን ጨምሮ በጥንታውያን ቅርሶቻችን አቅራቢያ ውጊያ ማድረግ በጥብቅ ሊወገዝ ይገባል! ** በወ | Ashara Media - አሻራ ሚዲያ

ላልይበላን ጨምሮ በጥንታውያን ቅርሶቻችን አቅራቢያ ውጊያ ማድረግ በጥብቅ ሊወገዝ ይገባል!
**
በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ!

አማራ ክልል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት እና ቅርሶች የተዋበ አካባቢ ነው። ከእነዚህ የኢትዮጵያውያን ጥበብ በጉልህ ከተገለጠባቸው ሥፍራዎች ውስጥ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባሕል ድርጅት የሆነው ዩኔስኮ በ፲፱፸፱ ዓ.ም በቅርስነት የመዘገበው የቅዱስ ላልይበላ አብያተ ክርስቲያናት ተጠቃሽ ናቸው። ቤተ ጊዮርጊስ (ባለ መስቀል ቅርፁ) እና ቤተ መድሃኔዓለምን ጨምሮ ፲፩ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን ያካተቱት የላልይበላ ቤተ እምነት እየሩሳሌምን ታሳቢ አድርገው በ፲፪ኛው መ.ክ.ዘ በንጉሥ/ቅዱስ ላልይበላ አማካይነት የተገነቡ ናቸው፡፡

እነዚህ የአባቶቻችን ጥበብ ጎልቶ የሚታይባቸው አካባቢዎች ላለፉት ምዕተ ዓመታት የአለም አቀፉን ሕብረተሰብ ልብ የሳቡ፣ ለአገራችን የገቢ ምንጭ ሆነው ያገለገሉ፣ የነፍስና የሥጋ ድህነትን የቸሩ እንዲሁም ጎሳና ሃይማኖት ሳይለያቸው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚኮሩበት ቅርሳቸው ነው።

ይሁን እንጂ የፌደራል መንግሥቱ ከሕወሓት ጋር ገብቶበት በነበረው ጦርነት በቅርሱ ላይ ተደቅኖበት ከነበረው አደጋና ስጋት ገና ሳያገግም፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ መንግሥት ከፋኖ ኃይሎች ጋር በገባው ጦርነት በቅርሶቹ አካባቢ የከባድ መሳሪያ ተኩስ ማከናወኑ መላውን የዓለም ማህበረሰብ እጅግ ከፍተኛ ስጋት ላይ ጥሏል። በተፈጸመው አስነዋሪ ድርጊትም ጥንታዊ ቅርሱ አስጊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ከአይን እማኝ የመረጃ ምንጮቻችን ለማረጋገጥ ችለናል። የሃይማኖታዊ መዳረሻ፣ የሰላምና ፍቅር መገኛ እንዲሁም ቅዱስ ስፍራ የሆነው ላልይበላን ጨምሮ ኹሉም ታሪካዊ ቅርሶቻችን የጦርነት ሥፍራ እንዲሆኑና ለአደጋ እንዲጋለጡ በየትኛውም መልኩ ሊፈቀድ አይገባም። ስለዚህ:-

፩. ዩኔስኮ "እጅግ የላቁ የዓለም እሴትና ቅርሶች ናቸው" ያላቸው ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ጥንቃቄና እንክብካቤ የሚሹ በመሆናቸው፤ መንግሥት በዓለም አቀፍ ሕግጋት መሠረት ቅርሶቹን ለጉዳት ከሚያጋልጡ ማንኛውም ድርጊቶች እጁን እንዲሰበሰብና ምንም ዓይነት ከባድ መሣሪያ በቅርሶቹ አካባቢ እንዳይጠመድ እንዲሁም እንዳይተኮስ እንጠይቃለን።

፪. የመንግሥት የጸጥታ አካላትም ሆኑ የፋኖ ኃይሎች በክልሉ በሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶች አቅራቢያ ውጊያ እንዳያካሂዱና የቅርሶቹን ህልውና አደጋ ላይ ከሚጥሉ ማናቸውም እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ አጥብቀን እናሳስባለን።

፫. የአካባቢው ማኅበረሰብ እነዚህን በምህንድስና ሥራ ዓለምን ያስደመሙ አብያተ እምነት ለብዙ መቶ ዓመታት ጠብቆ እንዳቆየ ሁሉ ዛሬም ይህን ኃላፊነቱን በላቀ ሁኔታ እንዲወጣና የኢትዮጵያ ሕዝብና የዓለም ማኅበረሰብ የጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ አጥብቀን እናሳስባለን።

በመጨረሻም ከዚህ ቀደም ደጋግመን እንደገለጽነው አገር ከምትገኝበት ችግር ብቸኛ መውጫ መንገድ ኹሉን አቀፍ፣ ግልጽና በአግባቡ የሚመራ የፖለቲካ ድርድር መሆኑን ዛሬም አጽንኦት ሰጥተን እየገለጽን፤ መንግሥት ለሰላማዊ መፍትሄ በሮቹን እንዲከፍት እናሳስባለን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያ እና ሕዝቧን ይጠብቅ!
እናት ፓርቲ
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ህዳር ፲፪ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም