Get Mystery Box with random crypto!

#እናቱ_እናቴ_ልደትሽ_ልደቴ ! ለእናትነት ክብር - እርሱ ከመረጠሽ በዮሐንስ በኩል - ለእኔ ከ | ደቂቀ እስጢፋኖስ ijoollee isxifaanoos🙏⛪️🙏

#እናቱ_እናቴ_ልደትሽ_ልደቴ !

ለእናትነት ክብር - እርሱ ከመረጠሽ
በዮሐንስ በኩል - ለእኔ ከተሰጠሽ
እኔም እርሱን ጌታ - ብዬ ከተቀበልሁ
ማዳኑን አምኜ - በሕጉ ስር ከዋልሁ
እናቱን እናቴ - ብየ ለመቀበል...
ጥያቄ ልደርድር? ለምን? እንዴት? ልበል?

ልጅሽ በምድር ላይ - ሥጋሽን በመልበስ
አዳምን ሊያድነው - ለእኛም ጽድቅን ሊያወርስ
የረገጠው መሬት - የቆመበት ቦታ
ከቤተልሄም ዋሻ - እስከ ጎለጎታ
ቅዱስ ከተባለ - ውሎ ያደረበት
ልዩ ክብር ካለው - የተሰቀለበት...
አንችማ እናቱ - ማህፀን ዓለሙ
የሰውነት ልኩ - ሥጋውና ደሙ
እንዴት አትከብሪ!? እንዴት አትቀደሽ!?
እንዴት አትወደጅ!? እንዴት አትወደሽ!?

እንኳንስ ለእኔና...
ለእርሱም ለጌታችን - ፈጣሪ ለሆነ
እናቱ መባልሽ - ይህ እውነት ከሆነ
እናቴ መሆንሽ - እንዴት አልታመነ???

በሥጋ ያይደለ - በረቀቀ መንፈስ
እናቴ ሆነሽኝ - ያንችን ክብር ብወርስ
ይሄንን መታደል - እንዴት እገፋለሁ?
እናቱ እናቴ ነሽ! - ተቀብየሻለሁ!!!

ፈጣሪን ልትወልጅው - አምላክን ልታ’ዥው
ሰማይና ምድር የማይወስኑትን - በእቅፍሽ ልትይዥው
ከድንግልና ጡት - ወተት ልታጠቢው
የዓለሙን መጋቢ...
ከደኃ ማጀትሽ - ሲራብ ልትመግቢው
እናት አባትሽን - ከእስር ልታስፈቺ
የክፋትን አባት - በፍቅር ልትረቺ
ከሀና ከኢያቄም - የተወለድሽ አንቺ
እናትና ድንግል - ንግሥትና አገልጋይ
ሰማየ ሰማያት - ጽርሐ አርያም ሆይ!
የአንቺ ግሩም ልደት - ለእኔም ነው ልደቴ
የጥምቀት መሥራቹ - ልጅሽ ነው አባቴ
ዳግም የተወለድሁ - ከውኃና መንፈስ
ባንቺ መወለድ ነው - የአዳም ተስፋው ሲደርስ
ሕይወት የሆነልን - የልጅሽ ሥጋና ደም
ከአንቺው ነው የነሳው - ከላይ አልወረደም
ዝም ማለት ያልቻልኩት - ለዚህ ነው ድፍረቴ
ልጅሽ ሕይወቴ ነው !
እናቱ እና ነሽ - ልደትሽ ልደቴ

ቅድስተ ቅዱሳን - ንጽሒተ ንጹሐን
ማሕጸኑ ለጽድቅ - እናቱ ለብርሃን
ሰማየ ሰማያት - ታናሽ ብላቴና
ከእያቄም ወሀና - ተወለደሻልና
ዓለም ብርሃን አየ - ውስጥሽ ባለው ፀሐይ
አዳም ቀና አለ - ተስፋ ብርሃኑን ሊያይ
ፍጥረታት በሙሉ - ከሰማይ ከምድር
በደስታ ተመሉ - ልደትሽ ሲነገር
ተወለደሻልና - የፀሐይ እናቱ
ጽርሃሐ-አርያም ሆንሽ - ብላቴናይቱ !

(አበው ስለክብርሽ - ቃላት አጠራቸው
ስለ ደም ግባትሽ - ምሳሌ ጠፋቸው
እኔ ግን ደፋሩ - እዘባርቃለሁ
ባልበሰለ ብዕር - ቃላት እመርጣለሁ
በተንሸዋረረ ዓይን - ክብርሽን አያለሁ
ምልጃሽን እያሰብሁ - በተስፋ እኖራለሁ።)

የብርሃን እናቱ - የፀሐይ ምሥራቁ
የአዳም ሙሉ ተስፋ - የሰይጣን መብረቁ
ስለ አንቺ መወለድ - ዓለም ተፈጠረ
ስለ አንቺ መወለድ - የሰው ልጅ ከበረ
አዳምና ዘሩ - በኃጢአት ቢረክሱ
በአንቺ መወለድ - ግን በክብር ነገሡ
በአንቺ ልዩ ልደት - አዳም አምላክ ሆነ
በአንቺ ልዩ ልደት - ክብራችን ገነነ
በአንቺ ልዩ ልደት - ዲያብሎስ ታሰረ
በአንቺ ልዩ ልደት - ባሪያ መሆን ቀረ
እኔም ደፋር ሆንኩኝ - ፍርሃት ተሰወረ
ባዶው አዕምሮዬ - ክብርሽን ነገረ፡፡

ሰማይና ምድር - ልደትሽን ሲያከብሩ
ሊቃውንት ሲቀኙ - መላእክት ሲዘምሩ
ክብርሽን ተማምነው - በምልጃሽ ያደሩ
በምህረት ቃል ኪዳን - ለክብር ሲጠሩ
እንደልጅነቴ ለእኔም - እንዲደርሰኝ
እንባሽን አስታውሶ - ልጅሽ እንዲምረኝ
ዝም ማለት ያልቻልኩት - ለዚህ ነው ድፍረቴ
የአንቺ መወለድ ነው - የጽድቅ መሠረቴ
ልጅሽ ሕይወቴ ነው !
እናቱ እናቴ ነሽ - ልደትሽ ልደቴ ነው፡፡


ምንጭ :- የተዋህዶ ልጆች ግሩፕ

እንኳን አደረሳችሁ

ደቂቀ እስጢፋኖስ


ሼር ሼር ሼር

ደስ የሚሉ የተዋሕዶ ትምህርቶችንና ግጥሞችን ለማግኘት ይሄንን ሊንክ ይንኩና join ይበሉ


https://t.me/mahibereestifanos111
https://t.me/mahibereestifanos111
https://t.me/mahibereestifanos111