Get Mystery Box with random crypto!

ትምህርት እና ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥርዓተ ትምህርት ከባሕላዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት | Ethiopian Digital Library

ትምህርት እና ኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥርዓተ ትምህርት ከባሕላዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር፣ በዋናነት ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር የተያያዘ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።

እ.አ.አ በ2015 በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዓመታዊ የትምህርት ኮንፈረንስ ላይ “የኢትዮጵያ የሥርዓተ ትምህርት መሠረት፣ ታሪካዊ፣ ፍልስፍናዊ፣ ሳይኮሎጂካል እና ሶሺዮሎጂካል ዕይታዎች” በሚል ርዕስ በወቅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ በነበሩት አወቀ ሺሺጉ የቀረበ ጥናት እንደሚያስረዳው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የትምህርት እሳቤ የተጀመረው በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ነው።

ጥናቱ ከሆነ እ.አ.አ በ1908 ዘመናዊ ትምህርት ወደ ኢትዮጰያ እስከገባበት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያን የትምህርት ሥርዓትን በስርዓቷ አቅፋ ይዛ እንደነበር ያትታል።

ዘመናዊ ትምህርትን ያስተዋወቁት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ በወቅቱ ባጋጠማት የማኅበራዊ ቀውስ ምክንያት ዘመናዊ ትምህርትን በ1908 ወደ ኢትዮጵያ ማምጣታቸውን ጥናቱ ያብራራል።

ዘመናዊ ትምህርት በኢትዮጵያ እ.አ.አ 1908 በአፄ ምኒልክ ሲጀመር፣ ዓላማውም የምዕራባውያንን ሐሳቦች እና ዘመናዊነትን የመማር ፍላጎት፣ የመንግሥት ባንክ ምሥረታ፣ የድልድይ ግንባታ፣ የሆስፒታሎች፣ የሆቴሎችና የባቡር ሀዲድ ግንባታ፣ የፖስታ አገልግሎት፣ በስልክ እና ወዘተ የመሳሰሉ ፈጠራዎች አስፈላጊነት በመሆኑ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት እንደነበር ጥናቱ ያስረዳል።

የመጀመሪያው ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ የተመራው በግብፃዊ ፕሮፌሰር የነበረ ሲሆን፣ በትምህርት ቤቱ ወደ 150 የሚጠጉ ብቸኛ ወንድ ልጆች ይማሩበት ነበር። ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ የመኳንንት ልጆች ሲሆኑ፣ ከተማሪዎቹ መካከል ልጅ ኢያሱ እና ተፈሪ መኮንን (አፄ ኃይለሥላሴ) እንደሚገኙበት ጥናቱ ያረጋግጣል።

ዘመናዊ ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ በተስፋፋበት በዚያ ወቅት ሥርዓተ ትምህርቱ እንደ ሳይንስ፣ ሂሳብ፣ ሥዕል፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ አረብኛ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና የቤት አስተዳደርን ያጠቃልል ነበር።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የትምህርት ሚኒስትር የተሾመው በልጅ ኢያሱ (1906-1909) ጊዜ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ በርካታ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መከፈታቸው ይነገራል።

በትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ እድገት የተመዘገበውም በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ (1923-1966) ጊዜ ነው።

እድገቱ በሁሉም የትምህርት ዘርፎች ማለትም የትምህርት መዋቅር፣ የመምህራን ሥልጠና፣ የትምህርት አስተዳደር እና ትብብር እንደነበር ጥናቱ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ትምህርት ሥርዓት መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር አብሮ የሚቀያየር ስለመሆኑ፣ በትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ እድገት አሳይቷል ከሚባልለት ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን መንግሥት ወዲህ እንኳን ያለውን በመንግሥታቱ መቀያየር አብሮ የሚቀያየረውን የትምህርት ሥርዓትና የትምህርት መዋቅር መመልክት በቂ ማስረጃ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ።

ምንጭ: አዲስ ማለዳ

@Ethiopian_Digital_Library
@Ethiopian_Digital_Library