Get Mystery Box with random crypto!

ከምንጊዜውም በላይ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ቋሚ ሲኖዶስ የጸሎት ጥሪ አቀረበ። የኢትዮጵያ ኦር | Ashara Media - አሻራ ሚዲያ

ከምንጊዜውም በላይ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ቋሚ ሲኖዶስ የጸሎት ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ‹‹ቤተ ክርስቲያናችን ልጆቿ በሰላም በፍቅር በታነጸ ዕለታዊ ሕይወት እንዲኖሩ በማድረግ ሰላም የደግነት ሁሉ አክሊል የመንፈሳዊ ምግባራት ዘውድ መሆኑን ስታውጅ መኖሯን የታሪክ መዛግብት፣ ዕውነትን ለመግለጥ የሚተጉ ጸሐፍት ከመቅድም እስከ ህዳግ ይመሰክሩላታል።›› ብሏል፡፡

‹‹የእውነትና የሰላም አምድ እንደመሆኗም በሀገራችን እየተከሰቱ ያሉ አለመግባባቶችንና የእርስ በእርስ ደም መፋሰሶች እንዲቆሙ የሰላም ጥሪ ከማድረግ ጀምሮ ምህላ፣ ጾምና ጸሎት በማወጅ እግዚአብሔር ለሀገራችንና ለሕዝባችን ሰላምን እንዲሰጥ ስትማጸን ቆይታለች።›› ብሏል መግለጫው፡፡

‹‹ሰላም የሚጸናው ማንኛውም ማኅበረሰብ እርስ በእርሱ በመተሳሰብና በፍቅር በእውነተኛ መግባባትና በፍትሕ በርኅራሄና በመከባበር አብሮ መኖር ሲቻል ነውና በወንድማማችነት መካከል ጠብን ከሚዘሩ ጥላቻንና መራራቅን ከሚያሰፉ ንግግሮችና ድርጊቶች በመቆጠብ ሁሉም የማኅበረ ሰብእ ክፍል ለሰላም በጸሎት እንዲተጋ›› ሲልም  ቋሚ ሲኖዶስ አሳስቧል፡፡

ከምን ጊዜውም በላይ ሰላምና ፍቅር በሀገራችን እንዲሰፍን በአንድነት ሆነን የምንሠራበት ወቅት ላይ በመሆናችን በመጪዎቹ ዐበይት በዓላት፣ በዘወትሩ መንፈሳዊ አገልግሎት ሁሉም በየደረጃው ያላችሁ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶችና አገልጋዮች በየዐውደ ምሕረቱ ሰላምንና እርቅን በመስበክ በሀገራችን ኢትዮጵያ ያለው ችግር እንዲወገድ፣ ማኅበራዊ ሰላም እውን እንዲሆን የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉ›› ሲል ቋሚ ሲኖዶስ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡