Get Mystery Box with random crypto!

በአራብሳ ኮንዶሚኒየም በተሽከርካሪ የታገዘ የወንጀል ድርጊት እየተፈፀመ መሆኑ ተገለፀ! በአዲስ አ | Addis መረጃ™

በአራብሳ ኮንዶሚኒየም በተሽከርካሪ የታገዘ የወንጀል ድርጊት እየተፈፀመ መሆኑ ተገለፀ!

በአዲስ አበባ ከተማ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አራብሳ ኮንዶሚኒየም ውስጥ ለሚፈጠሩት የስርቆት እና የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ምክንያቱ የፖሊስ ጣቢያ በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ መሆኑን የአካባቢው የሰላም ሰራዊት አስታውቋል፡፡

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የአራብሳ ኮንዶሚኒየም የወረዳ አራት የሰላም ሰራዊት አስተባባሪ አቶ አደመ ደምሴ ለብስራት ሬድዮና ቴሌቭዥን እንደተናገሩት በአካባቢው የሚፈፀሙ ወንጀሎች እየተበራከቱ እንደሆኑ በመግለፅ በተሽከርከሪ የታገዘ የወንጀል ድርጊት እንደሚፈፀም ተናግረዋል

ወንጀሉን ፈፃሚዎቹ ቪትስ እና መሰል ተሽከርካሪዎችን እየተከራዩ ከሶስት ሰው በላይ በመሆን በነዋሪው መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ በስለት በማስፈራራት የሴቶችን ቦርሳ እና የወንዶችንም ስልክ እና ብር ይዘርፋሉ፡፡ እንዲሁም ወንጀለኞቹ ከሌላ አካባቢ እንደሚመጡ እና ከመኪና በተጨማሪ በባጃጅ ነዋሪውን አሳፍረው ወደ ሌላ ቦታ በመውሰድ ስርቆት እንደሚፈፅሙ ገልፀዋል፡፡

ለዚህ ወንጀል መበራከት ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ አንድ ፖሊስ ጣቢያ ለሁለት ወረዳ አገልግሎት ስለሚሰጥ እና የፖሊስ አባል እጥረት በመኖሩ እና በቂ የመንገድ ብሎም የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት አለመሟላት አስተዋጽኦ አድርጓል።

የመንገድ መብራት እንዲሰራ ብንጠይቅም መፍትሄ ግን እስካሁን አልተሰጠውም ብለዋል፡፡ወንጀሉም ጨለማን ተገን በማድረግ እየተሰራ እንደሆነ እና በአካባቢው ያለው የሰላም ሰራዊትም ሁሉም የቤተሰብ ሀላፊ ስለሆነ እስከተወሰነ ሰዓት ድረስ ብቻ እንደሚጠብቅ አክለዋል። እስካሁን በሰው ህይወት ላይ የደረሰ አደጋ ባይኖርም ለነዋሪው ግን በሰላም ወጥቶ መግባቱ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን አቶ አደመ ደምሴ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

Via Bisrat FM
@Addis_Mereja