Get Mystery Box with random crypto!

የድህረ-ምረቃ ፕሮግራም የመግቢያ ፈተናን በተመለከተ ከትምህርት ሚኒስቴር የተሰጠ መግለጫ በ2 | Payback Ethiopia

የድህረ-ምረቃ ፕሮግራም የመግቢያ ፈተናን በተመለከተ ከትምህርት ሚኒስቴር የተሰጠ መግለጫ

በ2016 ዓ.ም የሚሰጠውን የድህረ-ምረቃ ፕሮግራም የመግቢያ ፈተናን በተመለከተ ተቋማትና ተፈታኞች ሊያውቋቸው፤ ሊከተሏቸውና ሊፈጽሟቸው የሚገቡ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ከትምህርት ሚኒስቴር የተሰጠ መግለጫ

የትምህርት ሚኒስቴር በየጊዜው የትምህርት ጥራትን የሚያረጋግጡና የትምህርት ውጤታማነትን የሚያሻሻሉ የተለያዩ የለውጥ አጀንዳዎችን በመቅረጽና ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል። እነዚህን የለውጥ ሰራዎች ደግሞ በሁሉም የትምህርት እርከኖች ደረጃ በደረጃ ማስፈጸም ያስፈልጋል። በመሆኑም እስካሁን ድረስ በተሠሩ ጅምር የለውጥ ስራዎች የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።

መንግስት በ2016 ዓ.ም ከያዛቸው የትምህርት የለውጥ ስራዎች መካከል አንዱ አገራዊ የድህረ ምረቃ ፕሮግራም የመግቢያ ፈተና እንደሚሰጥ በቁጥር 1/256/539/15 ሐምሌ 20 ቀን 2015 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ማሳወቃችን ይታወሳል።

ስለሆነም ፈተናውን በተያዘለት እቅድና ጥራት ለማከናወን ይቻል ዘንድ ተቋማትና ተፈታኞች ሊያውቋቸው፤ ሊከተሏቸውና ሊፈጽሟቸው የሚገቡ አቅጣጫዎች እንደሚከተለው ተቀምጧል።

1. የድህረ ምረቃ የመግቢያ ፈተናው ከመስከረም 21–23/2016 ዓ.ም በሁሉም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በበየነ-መረብ የሚሰጥ መሆኑ፤

2. ተፈታኞች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ Graduate Admission Testing (GAT) የመመዝገቢያ ፖርታል https://portal.aau.edu.et ከመስከረም 11–20/ 2016 ዓ.ም ድረስ በበይነ መረብ ማመልከት የሚገባቸው መሆኑ፤

3. ተፈታኞች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመግቢያ ፈተና (GAT) የመመዝገቢያ ፖርታል ገብተው ሲያመለክቱ የመፈተኛ ጣቢያቸውን (ዩኒቨርሲቲ) እና ሌሎች መረጃዎችን በትክክል እንዲሞሉ እና መረጃ በትክክል እንዲደርሳቸው ማድረግ፤

4. ተፈታኞች ለፈተና ሲያመለክቱ ፈተናውን ለመውሰድ የሚከፈለውን ክፍያ ብር 1000.00 (አንድ ሺህ ብር) በቴሌ ብር እንዲከፍሉ ከወዲሁ የቴሊ ብር አካውንት መክፈት እንደሚገባው መረጃው በትክክል እንዲያውቁ ማድረግ፤

5. ተቋማት ለመማር ያመለከቱና የሚያመለክቱ አመልካቾችን በበየነ መረብ አንዲያመለክቱ እንዲሁም የፈተና ፕሮግራምና ተያያዥ መረጃዎችን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ድረ ገጽና ፖርታል ፤ www.aau.edu.et and https://portal.aau.edu.et ብሎም ኦፊሽያል ቴሌግራም ቻናል፤ Testing Center IER እንዲያገኙ መረጃውን በትክክል መስጠት፤

6. በየትኛውም የመፈተኛ ማዕከላት ለፈተና ለመቀመጥና ፈተናውን ለመውሰድ ተፈታኞች ፎቷቸው ያለበት Test Admission Ticket (TAT) ይዘው መገኘት ያለባቸው መሆኑ(https://portal.aau.edu.et/Web/ApplyForAdmission/Test Taker)

7. የመግቢያ ፈተናው በመላ ሀገሪቱ ባሉ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ በበየነ መረብ የሚሰጥ በመሆኑ ከኢንተርኔት ጋር የተገናኙ ኮምፒዩተር ያላቸው የመፈተኛ ማዕከላት Safe Exam Browser (SEB) ተጭኖባቸው Corrective and Preventive Maintenance ተደርጎላቸው እንዲሁም Power Backup እንዲኖራቸው ተደርጎ ከመውጫ ፈተና በተገኘው መልካም ተሞክሮ መሰረት አስፈላጊ ግብዓቶች ከወዲሁ ዝግጁ ማድረግ፤

8. ፈተናው በዩኒቨርሲቲዎች ኔትወርክ ብቻ የሚሰጥ በመሆኑ ይህንኑ የየዩኒቨርሲቲው አይሲቲ ዳይሬክተር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር እንዲያስፈጽም መመሪያ እንዲሰጥ፤

9. ከተፈታኞች ከሚሰበሰብ ከፍያ ውስጥ ለየዩኒቨርሲቲዎቹ የሚደርሰውን ድርሻ በቴሌ ብር አማካኝነት በቀጥታ ለዩኒቨርሲቲዎች የውሰጥ ግቢ አካውንት ገቢ የሚደረግ በመሆኑ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የቴሌ ብር አካውንት እንዲኖራቸው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመስራትና በመክፈት፤ የውስጥ ገቢ የንግድ ባንክ አካውንታቸውን እንዲሁም ለዚህ ጉዳይ አንድ Focal Person በመምረጥ ሙሉ መረጃውን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እስከ መስከረም 5 ቀን 2016 እንዲልኩ፤

10. የመግቢያ ፈተናውን የትምህርት ሚኒስቴርና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋራ የሚያስተዳድሩ እና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የሚሰጥ መሆኑን፤

11. የፈተናውን ውጤት ተፈታኞች ፈተናቸውን ሲጨርሱና በመጨረሻ መልሳቸውን ሲያስገቡ ወዲያውኑ ማየት የሚችሉ መሆኑን፤

12. ተፈታኞች የፈተናውን ውጤት የሚያሳይ ሰርተፊኬት ወረቀት (Hard Copy) አትመው መውሰድ የሚችሉ ሲሆን ለመማር በሚያመለክቱበት ተቋም ሰርተፊኬቱን ማቅረብ የሚችሉ መሆኑ፤

13. የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች የመግቢያ ፈተና ማለፊያ ነጥብ በትምህርት ሚኒስቴር የሚወሰን መሆኑ፤

ይህ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን የመግቢያ ፈተና ያላለፉ ተማሪዎችን ተቋማት የማይቀበሉ መሆናቸው፣ ያለፉ ተማሪዎችን ሲያበላ ደግሞ ሌሎች የመግቢያ መስፈርቶችን የሚያረጋግጡ መሆናቸው እንዲሁም በተቋማትና በትምህርት ክፍል ደረጃ ጭምር በየተቋማቱ የውስጥ አሰራር መሰረት ሌሎች ፈተናዎች እና መመዘኛ መስፈርቶች የሚሰጡ መሆኑን እያሳወቅን፤ ከላይ በተገለጹት አቅጣጫዎች መሰረት ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነትና ሚና እንዲወጡ እናሳስባለን።

ከሰላምታ ጋር!!

ትምህርት ሚኒስቴር